ጥንታዊው ደንጊያ


ከሃምሳ እስከ ዘጠና ፐርሰንቱ የዓለም ቋንቋ በሚቀጥለው መቶ ክፍለ ዘመን (century) ከምድረ ገጽ ይጠፋል ተብሎ ይገመታል!
Rosetta Stone
   ሮዜታ (Rosetta)!!! ስሙ ደስ ይለኛል፡፡ ተፈጥሮ ዝናብ አዝንቦ ያሳደገው አበባ ነገር አይመስልም? በእርግጥ ይመስላል ነገር ግን አይደለም! ስሙ ለጥንታዊው ደንጊያ የተሰጠ መጠሪያ ሲሆን የዓለም ቋንቋዎች ማከማቻ (storage) የሆነው ፕሮጀክት የዚህን ጥርብ ድንጋይ ቅርስ ስም ወርሶአል፡፡ የሮዜታው ድንጋይ በጥንታዊው ግብፅ ሮዜታ (ራሺድ) በምትባል ትንሽ የከተማ መንደር ውስጥ ፈረንሳያዊው ወታደር 1799 ዓ.ም. ምሽግ ለመቆፈር በሄደበት ወቅት የተገኘ  ሲሆን የተቀረፀው ግን ከክርስቶስ ልደት በፊት 186 ዓመተ ዓለም እንደነበረ ይነገርለታል፡፡ በላዩ ላይ የሄሮግላፊክስ ፅሁፎችን ከራሱ ጋር ጨምሮ በሦስት ቋንቋዎች (hieroglyphic, demotic and Greek) ተተርጉሞበታል፡፡ ማስታወሻነቱም የግብፅ ቀሳውስቶች መሪ የነበረው ፈርኦን (Pharaoh) ለግብፅ ህዝቦች እና ቀሳውስቶች ያደረገውን በጎ ስራ የሚተነትን ጽሑፍ ይዞዋል፡፡ ሰሞኑን የዶለቱብንን አስታውሳችሁ ብቻ ፅሁፉን ማንበብ እንዳታቋርጡብኝ ቶሎ ብዬ ሮዜታን ከቴክኖሎጂው ጋር የተያያዘበትን ጉዳይ ላውጋችሁ፡፡
በጥሩ ሁኔታ የተመረተ እና በጥንቃቄ የያዝነውን የወረቀት መረጃ ከ 1000 እስከ 2000 ዓመታት ሊቆይ ይችላል ይላሉ፡፡ ስለ አህዛዊ መረጃ (Digital Information) ማስቀመጫ ግን ይህን ማለት አንችልም፡፡ ፍሎፒ ዲስክ በመባል ይታወቀው  የነበረው ውሂብ ማከማቻ (Data storage) ከዚህ በፊት ታዋቂ የነበረበትን ጊዜ አብዛኞቻችን የምንዘነጋው አይመሰለኝም ዛሬ ግን ከምደረ ገፅ ጠፍቶአል ወይም በፕላስቲክ ሲዲ/ዲቪዲ ለረጅም  ግዜ አትመን (Burn) ሳንጠቀምባቸው ብናስቀምጣቸው የማግኘታችን ነገር አጠራጣሪ ይሆናል፡፡ በየግዜው አዳዲስ ቴክኖሎጂዎች ቢፈጠሩም የፅሁፍ ቅርሶቻችን እስከዘላለሙ ጠብቆ የሚያቆይ ማከማቻ እሰከ ቅርብ ጊዜ ድረስ አልተገኘም ነበር፡፡
Rosetta Disk
አስተማማኝ የማስተላለፊያ እና የማስቀመጫ መንገድ ካልተገኘ በስተቀር አንድ ህብረተሰብ ሰለ መቶ ዓመታት (Centuries) እንዴት ማሰብ ይችላል?  ይህ ነበር ዘ ሎንግ ናው ፋውንዴሽን በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎችን አሰባስቦ የተለያዩ የቋንቋ ታሪኮችን እና የፅሁፍ ቅርፆችን የማቆያ ፕሮጀክት ለማስጀመር ያነሳሳው፡፡ ከ 8 ዓመት ትጋት በኃላ ያሰቡትን ለማሳካት የበቁት እነዚህ ሰዎች ሲናገሩ ዲስኩን ለመፈብረክ በመቶዎች የሚቆጠሩት ሲሳተፉ የተለያዩ ቋንቋዎችን አሰባስቦ Scan አድርጎ ማዘጋጀቱ ላይ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ተካፍለውበታል፡፡ ይህ መረጃ የማሰባሰቡ ጉዳይም ከፕሮጀክቱ በጣም አስቸጋሪው ክፍል እንደነበር ተናግረዋል፡፡ በስተመጨረሻም የ1000 ሃገራት ቋንቋን 15,000 ገፅ  ብቻ የያዘ መረጃዎች ማከማቻ ዲስክ (Rosetta Disk) በማስቀመጥ የመጀመሪያ ስራቸውን ለማጠናቀቅ በቅተዋል፡፡ የዲስኩ ልኬት 3 ኢንች ስፋት ያለው ከመሆኑም በተጨማሪ እያንዳንዱ ገጽ 0.019 ኢንች ማለትም 5 የፀጉር ዘለላዎች ወደ ጎን ተሰድረው እርዝመት አለው እላዩ ላይም በ 8 ቋንቋዎች እና የፊደላት አጣጣል ”የዓለም ቋንቋዎች (Languages of the world)“ የሚል ተጽፎበታል፡፡ ለጥንቃቄው ሲባልም 4 ኢንች የሆነ የእንቁላል ቅርፅ ያለው መያዣ የተዘጋጅለት ሲሆን የሚያስገርመው ዲስኩ ያለምንም ተጨማሪ እንክብካቤ 2,000 እስከ 10,000 ዓመታት ይዞታውን እንደጠበቀ ይቆያል ብለዋል፡፡ ሌላው የሚያስደንቃችሁ ነገር የሮዜታ ፋይሎች አህዛዊ (Digital) አለመሆናቸው ነው፡፡ ምክንያቱም 15,000 ገፁን በየተራ ለማንበብ የሚያስችል 750 ያህል የማሳደግ ሃይል ያለው ኦፕቲካል አጉሊ መነፅር (Microscope) መጠቀም ይኖርብናል፡፡
የዚህን ጽሑፉ ውርጅናሌ ዲስክ ምድር ላይ አናገኘም ምክንያቱም በ 2004 በተላከው እና በአውሮፓዊያን የጠፈር ምርምር ጣብያ አማካኝነት ከሮዜታ የህዋው መርከብ ጋር አብሮ ወደ ጠፈር የሄደ ሲሆን  እንዳሰቡት ከተሳካላቸው 2014 ዓ.ም. አንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር ከተዘጋጁት አራት ተመሳሳይ ቅጂዎች መካከል አንዱ ኮሜት ላይ ይደርሳል ተብሎ ይገመታል፡፡ ይህ የስለላ ጣብያ የኮሜትን የሞሎኪዩል ቅንብሮች መጠን የሚለካ ሲሆን የፀሃይን ምዕዋር ለሚሊዮኖች አመታት ይዞራታል ተብሎ ያገመታል፡፡ የቀሩት ቅጂ ዲስኮች የቋንቋው ጥበቃ ለሚያሳስባቸው ተቋማት በ 25,000 የአሜሪካን ዶላር  ለሽያጭ የቀረቡ ሲሆን ወደፊት በብዙ ኮፒዎች ሊሰሩ እንደሚችሉ አስታውቀዋል፡፡ እንደ አለመታደል ሆኖ አማርኛ ቋንቋ እዛ ውስጥ መኖር አለኖሩን ማረጋገጥ አልቻልኩም፡፡
ሠላም ሁኑ
በይነመረብ ከተባለው መጽሐፍ አዘጋጆች የተወሰደ

Rosetta Disk Container
  


No comments: